የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ፍኖተ–መርህ ማጠቃለያ
መግቢያ፡
ይህ ፍኖተ-መርህ (ማኒፌስቶ) የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የትጥቅ ትግል ፕሮግራም ነው። የአማራ ሕዝብ ከሃምሳ ዓመታት በላይ በተከታታይ ሥርዓቶች የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የዕኩልነት እጦት፣ የፍትሕ መነፈግ እና የፖለቲካ መገለል ደርሶበታል። የአማራ ሕዝብ ለሀገር ግንባታ እና ኅልውና መጠበቅ የከፈለው ዋጋ በሃሰት ትርክት ተተርጉሞ ለጥቃት እንዲጋለጥ ተደርጓል። አፋሕድ ይህን የጥፋት ዘመቻ ለመቀልበስ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ትግል እያደረገ ይገኛል። የአማራ ሕዝብ ለተደረሰበት ግፍ ሌሎች ሕዝቦችን ተጠያቂ አያደርግም፤ ይልቁንም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር ለእኩልነት እና ለሰላም ይታገላል።
አማራ የካበተ ታሪክ ባለቤት ነው። ከዳማት ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የሀገር ግንባታ እና ስልጣኔ ባለቤት ነው። ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የግዛት አንድነት ገንብቷል። የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት እና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶቹ ምስክሮች ናቸው። የአማራ ሕዝብ በየጊዜው ከውጭ እና ከውስጥ የተቃጡ ጥቃቶችን ተቋቁሞ ሰፊውን ድርሻ በመወጣት ሀገርን ከነ ሙሉ ክብሯ ለትውልድ አስረክቧል፣ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነትም የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ነገር ግን የአማራ ሕዝብ ላለፉት ተከታታይ ሥርዓቶች በውጭ ጠላቶች በተሸረበበት ሴራ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንዲሉ ፀረ-አማራ ትርክት በመፍጠር ሁለገብ ጥቃት ተከፍቶበት ይገኛል። በርካታ መስዋዕትነት ከፍሎ አፋኙን የኢሕአዴግ ሥርዓት ቢገረስስም ብአዴንና ኦሕዴድ ትግሉን ጠልፈው ለሌላ ዙር መከራ ዳርገውት ይገኛሉ። በአሁኑ ስዓትም በዐብይ አሕመድ መሪነት የብልጽግና ሥርዓት የአማራን ኅልውና ለማጥፋት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን አፋሕድ ይህን ለመቀልበስ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የትጥቅ ትግል እያደረገ ይገኛል።
ምዕራፍ አንድ: የትጥቅ ትግል መነሻ እና ግብ
መነሻ: የአማራ ህዝብ ለሀገር ግንባታ የተጫወተው ሚና እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ታሪኩ እና ባህሉ በሀሰት ትርክት እንዲጠፋ ተደርጓል። በኢሕአዴግ ዘመን የዘር ማጥፋት ወንጀል በበደኖ፣ ወለጋ፣ መተከል እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጸመ ሲሆን አማራን የማጥፋት እቅድ በብልጽግና ዘመንም ተባብሶ ቀጥሏል። ከጥቂት ወራት በፊት ጦር አዝምተው ተነግሮ የማያልቅ ግፍ የፈጸሙበት ኃይሎች ከነሙሉ አቅማቸው አያሉና ለሌላ ዙር ጥቃት የተዘጋጁ በነበሩበት (እና አሁም ባሉበት) ሁኔታ፤ አገዛዙ የአማራ ሕዝብ ወረራውን የመከትለትን ልዩ ኃይል በተለየ ሁኔታ እንዲፈርስና ትጥቁን እንዲፈታ ካደረገ በኋላም የፋኖንና የአርሶ አደሩን መሣሪያም ለመሰብሰብ ወደ ተግባር የገባው ያለማንም ከልካይ አማራ የሚባልን ሕዝብ ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት መሆኑ ግልፅ ነበር። ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ የኅልውና አደጋ ውስጥ መውደቁ፣ ፖለቲካዊ ክህደት መፈፀሙ፣ ህዝቡ በተደጋጋሚ ለሚያነሳቸው የማንነት እና የፖለቲካ እንዲሁም የመልማት ጥያቄዎች መልስ አለመስጠት፣ ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ በማንነቱ የሚደርስበት ግፍና በደል እንዲሁም የኅልውና ዘብ የሆነውን ልዩ ኃይልና ፋኖ እንዲበተን በማድረግ በመላ ሕዝቡ ላይ መንግሥት መር ጭፍጨፋ እንዲካሄድበት መደረጉ የትግሉ መነሻ መሰረታዊ ምክንያቶች ናቸው።
ግብ: የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የዘር ማጥፋት መቀልበስ፣ ኅልውናን ማረጋገጥ፣ የማንነት እና የግዛት ጥያቄዎችን መመለስ፣ እርቅ እና የሽግግር ፍትሕ፣ ጸረ-አማራና ሀገር አፍራሽ የሆነውን ሕገ-መንግሥት እና ትርክት መቀየር፣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ ፍትሕና እኩልነት ማረጋገጥ፣ ለዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በትብብር መሥራት የትግሉ ግቦች ናቸው።
ምዕራፍ ሁለት: ቁልፍ መርሆዎች
አፋሕድ ግቡን ለማሳካት ቁልፍ መርሆችን ይከተላል። ከነዚህ መርሆች ዋናዎቹ እኩልነት እና ነጻነት፣ የሃይማኖት እና መንግሥት መለያየት፣ በትብብር መሥራት፣ የጋራ ጥቅም፣ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና የዓለም አቀፍ ደንቦችን ማክበር ናቸው።
ምዕራፍ ሦስት: ፕሮግራሞች
የፖለቲካ ፕሮግራም:- ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ተራማጅ የሆነ ርዕዮተ-ዓለም መከተል፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣በውይይት የሚወሰን የመንግሥት አወቃቀር፣ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት፣ የሕዝብ ጥቅምን ማስቀደም፣ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ዋና ዋናዎቹ የፖለቲካ ፕሮግራሞቹ ያጠነጠነባቸው ጉዳዮች ናቸው።
የኢኮኖሚ ፕሮግራም:- በጦርነት ለተጎዳው የአማራ ሕዝብ ተመጣጣኝ የማካካሻ ፕሮግራም፣ ሀገር አቀፍ ጉዳዮችንም በተመለከተ፤ የሰው ሀብት ልማት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጫ ፕሮግራሞችን መዘርጋት፣ ኢንዱስትሪና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ ግብርናውን ማዘመን እና ነጻ ገበያን ተግባራዊ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ በኢኮኖሚ ፕሮግራሙ የተካተቱ ናቸው።
ማኅበራዊ ፕሮግራም:- ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ እና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር፣ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና ፕሮግራም መዘርጋት፣ ለዘርፈ ብዙ ዕድገት ጠቀሜታ ያላቸውን የሕዝብ እሴቶችን መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ ትኩረት የሚደረግባቸው ማኅበራዊ ፕሮግራሞች ናቸው።